የኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ ፤ ሌላ የማንም አይደለሁም ፤ የፈጠረኝ እርሱ ፣ ያዳነኝ እርሱ ፣ የመጣልኝ እርሱ ፣ የተገረፈልኝ ፣ የተቸነከረልኝ ፣ እርቃን የታየልኝ ፣ ደሙን ያፈሰሰልኝ እርሱ ፣ የሞተልኝ ፣ በመቃብር ያደረልኝ ፣ የተነሳልኝ ፣ ያረገልኝ እርሱ ፣ በሰማይ ያለ ሊቀ ካህኔ እርሱ ፣ ዋሴ ጠበቃዬ መካከለኛዬ አስታራቂዬ ፣ መጥቶ የሚወስደኝ እርሱ፣ ሁሉ በጌታዬ ተጠናቆልኛል የኔ አባት ጀግና ነው በሁለንተናው ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአለም በቂ እና ከበቂ በላይ በላይ ነው አዳኝ ነው ብቻውን። ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1: 15) ።
ሲፈጥረኝ ብቻውን ነው የፈጠረኝ የሰው እርዳታ አላስፈለገውም ፣ ሲያድነኝም ብቻውን ነው ያዳነኝ ወይ ችንካሩን ወይም ግርፋቱን ያገዘው የለም። አልቀላውጥም እኔን ለማዳን አባቴ ብቻውን ብቁ ስለሆነ ተጨማሪ የመዳኛ መንገድ ፍለጋ አልቀላውጥም። ያውም ቅልውጥና አያጠግብም እኮ አያረካም እኮ ከእዛ እዚህ ከእዚ እዛ ያስብላል ቅልውጥና የዘወትር ምግብ አይሆንም ቅልውጥና እረፍት የለውም ።
ኑ እና በዚህ ጌታ እርፍፍፍፍፍፍ በሉ ካዳናችሁ ጌታ ጋር አዲስ ኪዳን ይኑራችሁ አዲስ ሕይወት ጀምሩ አሮጌውን ጥላችሁ ያማረውን ነጩን ልብስ የማያረጅ የማያድፈውን ዘለአለማዊ የጽድቅ ልብሳችሁን ልበሱ። የማትቀሙትን ፀጋ የማታጡትን እረፍት የማያሳዝነውን ደስታ የማይጠፋውን ሰላም የማይደበዝዘውን የቅድስና ብርሃን በስፍራ እና በቦታ ያልተገደበውን ከሞት በኋላ ላለን ሕይወት አስተማማኝ ዋስትና የሆነውን ፤ ከኃጢአት እና ከሲዖል የሚያድን ፣ ደግሞ ከጨለማ እና ከኩነኔ የሚታደግ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በደጃችሁ ቆሟል .. አዲሱን ኪዳን ከእርሱ ጋር አድርጉ።
ዓለም እረፍት አልሰጠችኝም ፣ ብዙ አይነት ሃሳቦችን እና እምነቶችን እከተላለሁ ከሞት በኋላ ግን የት እንደምሄድ አላውቅም እያላችሁ የሞታችሁን ቀን በፍርሃት እያሰባችሁ ምትኖሩ ፣ ከሞት በኋላ የእግዚአብሔር እቅፍ ሳይሆን ሲዖል የሚታያችሁ ፣ እያደረጋችሁ ባላችሁት ኃጢአት ሕሊናችሁ ሰላም አጥቶ ዘወትር ጠላት የሚከሳችሁ ፣መዳን እፈልጋለሁ ፣ መቅበዝበዝ ሰልችቶኛል የምትሉ ኑ የሚወዳችሁ ጌታ አለ ፤ ኑ ከዚህ ሁሉ የሚያስጥላችሁ አዳኝ ጌታ አለ ፣ በክንፎቹ ጥላ ስር ማደር ይሆንላችኋል ኢየሱስ ክርስቶስ ይወዳችኋል። ይህንን የቃል ኪዳን ፀሎት አምናችሁ አብረን እንፀልያለን ... በቅንጣት ሰከንድ ውስጥ የዘመናት ሸክማችሁን እግዚአብሔር ከላያችሁ ያንከባልላል።
እንፀልይ ..
እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ፤ አንድያ ልጅህን እኔን ለማዳን ወደ ምድር እንደላክኸው አምናለሁ ፤ ከኃጢአት እና ከዘለአለም ሞት ሊያድነኝ ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኔ እንደተሰቀለ እንደሞተ አምናለሁ ፤ እኔን ስለማፅደቅም በሶስተኛው ቀን ከሞት እንደተነሳ አምናለሁ ፤ ወደ አንተ ወደ አባቱ ስፍራን ሊያዘጋጅልኝ እንደሄደ ዳግመኛም እርሱ ወዳለበት ሊወስደኝ እንደሚመጣ አምናለሁ፤ ዓለምን እክዳለሁ ፣ ሰይጣንን እክዳለሁ ፣ ዛሬ እውነትና መንገድ ሕይወትም በሆነው በአንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አንተ እቀርባለሁ ፣ የልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአቴ ሁሉ ያንፃኝ፣ አንተ አባቴ ነህ ልጅህ ስላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ነኝ ፣ በስራዬ ሳይሆን በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስራ ምክንያት በቀኝህ ስላስቀመጥከኝ አመሰግንሃለሁ ። ዛሬ ከቅዱስ መንፈስህ ስለተወለድኩ አመሰግንሃለሁ። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን።
የቅርብ ቀን አስተያየቶች :
ESHET
1208 days ago
የጌታ ስራ ይብዛልህ 🙏